እንኳን ደህና መጡ! (ስለኮሚቴው)

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሀገር ውስጥ እና በውጭው ዓለም በአጠቃላይ አርባ አራት አህጉረ ስብከቶች አሏት፡፡

የደቡብ ኦሞ ሀገረ ስብከትም በሀገር ውስጥ ከሚገኙት አህጉረ ስብከቶች አንዱ ነው፡፡ ሀገረ ስብከቱ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በደቡብ ኦሞ ዞን የሚገኝ ሲሆን መንበረ ጵጵስናውም ከአዲስ አበባ 781 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኝ በጅንካ ከተማ ላይ ነው፡፡
የሀገረ ስብከቱ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ እና የሕዝቦቹ አሰፋፈር በሰፋፊ ሜዳዎችና ሰንሰለታማ ተራራዎች የተከበቡ በመሆናቸው ቦታውን የተመለከተ ሁሉ እንደ ቅዱስ ዳዊት “እግዚአብሔርን ሥራህ ግሩም ነው በሉት” እንዲል ያስገድደዋል፡፡ የሕዝቡም እምነት ጠንካራና ከትውልድ ትውልድ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ በአለት ላይ የተመሠረተ መሆኑም ያኮራል፡፡

በደቡብ ኦሞ ዞን 440,623 የሚጠጉ ሕዝቦች ያሉ ሲሆን ከነዚሀም ውስጥ 107,280 ተጠምቀው የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮች ሲሆኑ፤ ሌሎች የተቀሩትም የሚያስተምራቸውና የሚያጠምቃቸው የሚሹና የሚናፍቁ ናቸው፡፡

በሀገረ ስብከቱ ሥር ዘጠኝ ወረዳዎች ያሉ ሲሆን በእነዚህም ወረዳዎች እስከ 1998 ዓ.ም ድረስ 29 አብያተ ክርስቲያናት ታንጸው የነበር ቢሆንም የአብያተ ክርስቲናቱ ቁጥር በሀ/ስብከቱ ከሚኖሩት ህዝቦች ብዛት አንጻር ተመጣጣኝ ባለመሆኑና በተለይም በገጠራማው የሀ/ስብረቱ አካባቢ ያሉ ወገኖች ከሚያስነሷቸው አስተምሩን አጥምቁን ቤተ ክርስቲያን ሥሩልን እኛንም እንደ እናንተ የክርስትና ህይወት ተካፋይ አድርጉን የሚለው ጥያቂያቸው እየበረከተ ከመምጣቱ የተነሳ ለዚህ ጥያቄ አፋጣኝ መልስ መስጠጥ አስፈላጊ ሆኗል፡፡