በዲ/ን አውራሪስ በላይ
ተወልደ ኢየሱስ በቤተልሔም ዘይሁዳ
አዋልደ ጢሮስ አሜሃ ይሰግዳ
ሰብአ ሰገል አምጽኡ ሎቱ ጋዳ
ወይተኃሠያ አዋልደ ይሁዳ
✟✟ እንኳን ለጌታችን ለአምላካችን ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት በሠላም አደረሳችሁ አደረሰን፡፡✟✟
ቤተ ክርስቲያናችን ከምታከብራቸው ዘጠኙ ዐበይት የጌታ በዓላት አንዱ ከሦስቱ አካል አንዱ አካል እግዚአብሔር ወልድ
በርሱ ፈቃድ በአባቱ ፈቃድና በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ በብስራተ መልአክ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም
በከብቶች በረት ለዓለም መድኃኒት ሊሆን በቤተልሔም የተወሰደበትን በዓለ ልደት ነው፡፡
✔የጌታችን ሰው ሆኖ መገለጡ
✥ ነበያት ውረድ ተወለድ ብለው ፤
✥ አበው በተስፋ ጽድቅህን ብርሃንን ኃይልን ላክልን ብለው የጮኹበት፣
✥ የአዳም ጸሎቱ ፍሬ ያገኘበት፣
✥ ሰው አምላክ አምላክ ሰው የሆነበት፣
✥ ሰውና መላእክት ሰውና እግዚአብሔር ሰማይና ምድር ህዝብና አሕዛብ የታረቁበት፣
✥ የክርስትና ሃይማኖት የመገለጥ ሃይማኖት መሆኗ የተመሠከረበበት
✥ እንዲሁም ሊቁ ሱኑቲዮ እንደተናገረው “ልደት ቀዳማዊ ተዐወቀ በልደት ደኃራዊ ” እንዳለ ቅድመ ዓለም ከአብ ያለ እናት መወለዱ ድኅረ ዓለም ከእናት ያለ አባት በመወለዱ የታወቀበት ዐቢይ በዓል ነው፡፡
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆነ በሥጋ ማርያም ተገልጦ በቤተልሔም በተወለደ ጊዜ በወቅቱ የነበረውን አቀባበል በአምስት ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡
1. የትጉሃን አቀባበል
2. የእንቅልፋሞች አቀባበል
3. የንፉጋን አቀባበል
4. የደንታቢሶች አቀባበል
5. የሠይፍ አቀባበል ናቸው፡፡
1. የትጉሃን አቀባበል
1.1የትጉሃን መላእክት አቀባበል
በዕለተ እሑድ የተፈጠሩ መላዕክት አምላክ ወልደ አምላክ የሆነ ጌታችን በተወለደ ጊዜ ነቅተውና ተግተው በቤተልሔም
ዙሪያ ተሰብስበው በምስጋና ተቀብለውታል፡፡ ከዚያም አልፎ የምስራቹን ለዓለም ተናግረዋል፣የመላአክትን ምስጋና
በተመለከተ ቅ/ያሬድ በአንቀጸ ብርሃኑ ሲገልጠው “ልጅሽንም በዚህ አለም በወለድሽው ጊዜ ዓይኖቻቸው ብዙዎች የሆኑ
ኪሩቤልና ክፍፎቻቸው ስድስት የሆኑ ሱራፌል በበረት ውስጥጋረዱሽ የብርሃን ደመናዎችም ከበቡሽ የመለአክት አለቆች
የመላእክት ሠራዊትና የሰማይ ጭፍሮች በመፍራትና በመንቀጥቀጥ በፊትሽ ቆሙ በዚህም ዓለም ኪሩቤልና ሱራፌል በሰማያት
ካለው ምስጋናቸው ወይም ከቀድሞ ምስጋናቸው ወገን ባልሆነ በሌላ /አዲስ/ ምስጋና አመሰገኑሽ ፍጥረትን ሁሉ ሰብስቦ
የያዘና ፍጥረቱን ሁሉ የሚመግብ ጌታቸው በብብትሽ /በክንድሽ/ ተቀምጦ ጡትሽን እንደ ህጻን ሲጠባ ባዩ ጊዜ በአርያም
ፈለጉና በዚህ ዓለም እንደቀድሞው ከአባቱና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር አገኙት የጌታ ትሕትናውን ባዩ ጊዜም ዓይኖቻቸውን
ወደ ላይ ወደ አርያም ከፍ ከፍ አደረጉ ክንፋቸውንም ዘርግተው ለሁሉ ጌታ ለአንተ ምስጋና ይገባል እያሉ ጌታቸውን
አመሰገኑ ዳግመኛም በዋሻ በጎል ውስጥ አንቺን ከሕጻንሽ ጋር አይተው በምድር ላይ ሠላም ፍቅር አንድነት ሆነ አሉ”
ብሎ አቀባበላቸውን ገልጾልናል፡፡
1.2 የትጉሃን እረኞች አቀባበል
በሉቃ 2፥8-20
እንደተገለጠው በሌሊት መንጋቸውን ይጠብቁ ለነበሩ እረኞች የእግዚአብሔር መልአክ ተገልጦላቸው የምስራቹን ዜና
በነገራቸው ጊዜ ይህን በጆሯቸው የሰሙትን በዓይናቸው ለማየትና ለማመስገን ተግተው ከእረኝነት ተግባራቸው በመነሣት
ወደ ቤተልሔም በመገስገስ ምስጋና አቅርበውና ሰግደው ከመላእክት ጋር በአንድነት በማመስገናቸው ቀድሞ በመጽሐፍ
እንደተነገረ “ዮም አሐደ መርዔተ ከኑ መላእክት ወሰብእ ከመይስብሕዎ ለክርስቶስ በቃለ አሚን” የተባለው መጽሐፋዊ
ቃል ተፈጸመ ዳግመኛም “የአዳም ምስጋና ከመላእክት ምስጋና ጋር አንድ ሆነ ምስጋናቸውም የተስተካከለ ሆነ ተብሎ
የተነገረው ቃል ተረጋገጠ” 3ኛመቃ 4፥11 በዚህም የእረኞቹ ተግቶ መቀበልና በተወለደበት ስፍራ መገኘት የመጽሐፍ
ቃል እንዲፈጸም አደረጉ የልደቱ እማኞችም ሆኑ፡፡
1.3 የእንስሳት አቀባበል
ቅ.ል.ከ ከ700
ዓመት በፊት ኢሳይያስ በትንቢቱ “በሬ ገዢውን አህያም የጌታውን ጋጣ አወቀ፤ እስራኤል ግን አላወቀም ሕዝቡም
አላስተዋለም ” ት.ኢሣ 1፥3 ብሎ እንደተናገረው ጌታችን አምላካችን በተወለደ ጊዜ ወራቱ ብርድ የጸናበት
እመቤታችንም ትጠቀልልበት ዘንድ መጠቅለያና ጨርቅ ያጣችበት በነበረ ሰዓት እንስሳት አህያ በሬ ላም ቢል ወገኑ አንድ
ነውና ጌታቸው መሆኑን አውቀው የሰጣቸውን እስትንፋስ ስጦታ አድርገው በመስጠት በልደቱ ተካፋይ ሆነዋል እስትንፋስ
በመለገስ መልካም አቀባበልም አድርገውለታል፡፡
1.4 የሰብአ ሰገል አቀባበል
ከ1000 ዓመት
በፊት ልበ አምላክ ዳዊት “የተርሴስ ደሴቶችና ነገሥታት ስጦታ ያመጣሉ የአረብና የሳባ ነገሥታት እጅ መንሻ ያቀርባሉ
ነገሥታት ሁሉ ይሰግዱለታል አሕዛብም ይገዙለታል ” መዝ 71፤10-11 እንዳለ ሦስቱ ነገሥታት ማንቱሲማር፣
ዲዲያስፋና ሜልኮስ የአባታቸውን የዘረድሸትን ቃል ሰምተውና የነገራቸውም ሲፈጸም ሦስቱም እያንዳንዳቸው 10 ሺህ
ሰራዊት አስከትለው ከሩቅ አገር በመምጣት ወርቅ እጣን ከርቤ እጅ መንሻ ገብረው በፊቱም ወድቀው ሰግደው አቀባበል
አድርገውለታል፡፡ማቴ 2፥1-13
2. የእንቅልፋሞች አቀባበል
ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል
ማርያም በቤተልሔም ሲወለድ ሌሊት እንደነበር ወንጌል ይነግረናል /ሉቃ2፥8-20/ ይህንን አስቀድሞ ትንቢት
የተነገረላቸው ሱባኤ የተቆጠረላቸው የአበውን ተስፋ ሲጠባበቁ የነበሩ በቅርብ ያሉ ሕዝበ እስራኤል ግን በዚህ የመዳን
ቀንና የምስራቹ ዜና በዓለም በታወጀበት ጊዜአንቀላፍተው በመገኘታቸው ክብሩን ግርማውን እንዳያዩና የሩቅ ሀገር
ሰዎች ቀድመው ተግተው በመገኘት ትንቢተ ነቢያት ሲፈጸም ተስፋ አበው ሲበሰር ከምስራቹ እንዲሳተፉ ሆነዋል፡፡ ለዚህም
ነው ቅዱስ ዮሐንስ በወንጌሉ ሲገልጽ እስራኤል ለዚህ ለበዓለ ልደቱ ለምስራቹ ዜና ስላልበቁና ለማየትም ስላልታደሉ
ወገኔ ብሎ ወደ እነርሱ ሲመጣ ላለመቀበል የወሰኑትና እስከ መስቀል ሞትም ያደረሱት ዮሐ1፥11
3. የንፉጋን አቀባበል
እመቤታችን ልጇን አምላካችንን ክርስቶስን ልትወልድ ባለች ጊዜ አውግስጦስ ቄሳር የተባለ ሃገረ ገዢ ሕዝብ ሁሉ
እንዲቆጠር አዋጅ አውጆ ነበር ሉቃ 2፥1 በዚህም በቤተልሔምና ዙሪያ ብዙ ሕዝብ ተሰብስቦ ማረፊያም ይዘው ነበር
እመቤታችንም በዚያ ሳለች በመውለጃዋ ሰዓት ሲደርስ አረጋዊ ዮሴፍ ማሳደሪያ እንዲሰጡት ሁሉን ቢጠይቅ እምቢ አሉ
አኃዜ ዓለም በእዴሁ የተባለ አምላክ የሚወለድበት ስፍራ አጥቶ ደጃፉን የሚከፍትለት ሰው አጥቶ የከብቶች በረት
ተወለደ በዚህም ክብር ከሰዎች ርቃ ለእንስሳት ሆነ፡፡
4. የደንታ ቢሶች አቀባበል
ይህ
አይነቱ አቀባበል የካሕናተ አይሁድ አቀባበል ነው እነዚህ በህዝብ ላይ ለማስተማርና ለመፍረድ የተሾሙ የኦሪትና
የነብያትን መጽሐፍት ጠንቅቀው የሚያውቁና ምስክር የሆኑ የሕዝብ መሪዎች የሚያውቁትን የሚተረጉሙትን ሕግ ሳይጠቅማቸው
ቀድሞውንም መጽሐፍ እንዳለ ዓላማቸው በክብር በስልጣን በመዐረግ ሰበብ የሕዝቡን ገንዘብ በመቀበል መክበር ነበርና
ይከብሩበትና ይመሰገኑበት የነበረውን አምላክ ሳይቀበሉት ከምስክርነቱና ከምስራቹ ሕይወት ፊት የራቁና የተለዩ
ሆኑ፡፡ማቴ 23፥14
5. የሠይፍ አቀባበል
ይህ አይነቱ አቀባበል የንጉሥ ሄሮድስ አቀባበል
ነው፣፣ ከሩቅ አገር የመጡ ሰብአ ሰገል /የጥበብ ሰዎች/ ኮከብ እየመራች አምጥታ ስትሰወርባቸው ንጉሥ ሁሉን ያውቃል
ብለው ሄሮድስን ከዓለም አስቀድሞ ንጉሥ የሆነውን ክርስቶስን በየት እንደተወለደ በጠየቁት ጊዜ ጉልበቱ ርዶ ልቡ
ደንዝዞ ቀርቶ ነበር ይሁንና ረበናተ አይሁድን ጠርቶ መልስ አግኝቶ ሰብአ ሰገልም ጠይቆ ዓመቱን ከተረዳ በኋላ ሄደው
አንዲሰግዱና እርሱም ለሰገደለት ወደ ርሱ እንዲያመጡ ጠይቆ ነበር ይሁንና መልአከ እግዚአብሔር ሰብአ ሰገል
ከቤተልሔም ተገኘው ከልደቱ ምስራች ተሳታፊ ከሆኑ በኋላ በሌላ መንገድ እንዲሄዱ ነግሯቸው ነበርና ሄደው ቢያጣቸዉ
144,000 ሕጻናትን ክርስቶስን እገድላለሁ ብሎ ደም አፍስሶ አስፈጃቸው እንዲህ ባለ አቀባበል ለዓለም መድኅን
ለቤዛ ዓለም የመጣን ክርስቶስን እንዲህ ባለ አቀባበል ተቀበለ፡፡
✔ከአቀባበሎቹ ምን እንማራለን
ከትጉሃን ተቀባዮች ስንመለከት በተለይ የእረኞች የሰብአ ሰገልና የእንስሳት አቀባበል ብዙ ነገር ያስተምረናል
❖ ከእንስሳት፡-
አላዋቂ ሆነው የተፈጠሩ እንስሳት ጌታችን በተወለደ ጊዜ ቤተልሔም+— እንደነበረች ተረድተው ሲፈጥራቸው
የሰጣቸውን ትንፋሻቸውን በመለገስ እንዳሟሟቁት እኛም አዋቂ ሆነን የተፈጠርን እርሱ እግዚአብሔር ወደ ፈቀደ ከሰጠን
ሀብት፤እውቀት፣ጉልበትና ጊዜን ለሰጠን ለእግዚአብሔር አምላክ መስጠት እና የሰጠህኝን ሰጠውህ ልንል ይገባል፡፡
❖ ከእረኞች፡-
እረኞች የተናቁ የተዋረደ ስራ ሰርተው የሚኖሩ ቢሆንም ኃላፊነታቸውን ባለመዘንጋት የሰሙትን የምስራች ቃል አይተው
ከምስጋናው ለመሳተፍ ወደ ቤተልሔም እንደገሰግሱ እኛም ም ቤተልሔም ተብላ በምትጠራ በበቤተክርስቲያን የምስራቹን
ወንጌል ለመስማት እና በቤተልሔም የተገኘውን ጌታችንና እመቤታችንን እንዲሁም እንደ ቅዱሳኑ አረጋዊ ዮሴፍና ሰሎሜን
ለማመስገን ፈጥነን ገስግሰን ወደ ቤተ ክርስቲያን ልንመጣ ይገባል፡፡
❖ ከሰብአ ሰገል፡-
እነኚህ የምድር ነገሥታት ናቸው ሀገር የሚያስተዳድሩ ፤ሕዝብ የሚመሩና በሠራዊት የሚታጀቡ ናቸው፡፡ ነገር ግን ይህ
ሁሉ ክብር ይህ ሁሉ ስልጣን እሾህ /ማነቆ/ ሳይሆናቸው አምላክነቱን ንጉሥነቱን አዳኝነቱን አውቀው እጅ መንሻ ይዘው
እንደመጡ ገዢነታችን ክብራችን ሳያሸንፈን ለምስጋና ለአበርክቶት ወደ እናትና ልጅ እንዲሁም ቅዱሳኑ ወደሚገኙበት
ወደ ቤተክርስቲያን ልንመጣ ይገባል፡፡
❖ ሰብአ ሰገል ቤተልሔም በደረሱ ጊዜ ጌታ የተወለደው ጭቃ
በበዛበት የከብቶች እዳሪ እበት ያጨማለቀው ቢሆንም ስፍራውን ሳይንቁ ወደው አጎንብሰው በመስገድ አንዳመሰገኑና እጅ
መንሻ እንዳቀበሉ እኛም ቤተልሔም የተባለች ቤተክርስቲያንን ስንወድንና ለአኮቴት ለአምልኮ ስንመጣ ከነ ችግሯ
መከራዋና ፈተናዎቿ ሁሉ መሆን ይገባል፡፡
✔ከእንቅልፋሞች አቀባበል
እነዚህ ትንቢት ተነግሮላቸዉ ሱባኤም ተቆጥሮላቸው ከቤተልሔም ቅርብ ሆነው ሳለ በስንፍናቸው ምክንያት ከምስራቹ ዜና
ተለይተዋል፤ እኛም በሃይማኖት ጸንተን ከቤተክርስቲያን ቀርበን ሳለ በዝንጋኤና ስንፍና ከተሰበከችልንና
ከምትሰበክልን ከምስራቿ የወንጌል ቃለ ትምህርት ርቀን ሩቅ የተባሉት ከሃዲያን መናፍቃን አሕዛብ ለምስክርነትና
ለክብር ለምስጋና እንዳይቀድሙን ተግተንና ነቅተን በቤተልሔም ቤተክርስቲያን ቀድመን ልንገኝና ምስክር ልንሆን
ይገባናል
✔ከንፉጋን አቀባባል
እነኚህ ሰዎች በከተማቸው በመኖሪያ መንደራቸው ሊደረግላቸው የታሰበውን ታላቅ ብስራት በራስ ወዳድነታቸውና ተቀባይና
አክባሪ ባለመሆናቸው አምላክችን ከእመቤታችን ጋር እንዲሁም ከቅዱሳኑ አረጋዊ ዮሴፍና ሰሎሜ ጋር ሲመጣ ላለመቀበል
በመወሰናቸው ሳይቀበሉ በራቸውን ዘግተው ተገኙ፡፡ ዛሬም የእውነት አምላክ የሆነ የክርስቶስን አምላክነት፣ አዳኝነት፣
እግዚአብሔርነት አምኖ ላለመቀበል፣ የወላዲተ አምላክን እናትነት አማላጅነትና ቃል ኪዳንነት ላለማመን በቅዱሳንን
ተራዳኢነትና አማላጅነት ላለመማጸን በመወሰን ማደሪያ የተባለ ልባቸውን የሚዘጉና ፍቃደኛ ላልሆኑ አማኞች ኋላ ኋላ
የእግዚአብሔር ክብር ርቃቸው ከእነርሱም ተለይታ በሃይማኖት ጎዶሎነት በምግባር ብሉሽነት እንስሶች ምሣሌ የሆኑላቸው
ከሃዲያን መናፍቃን አሕዛብ ይከብሩባታል ይመሰገኑባታል ማለት ነው፡፡
✔ከደንታ ቢሶች አቀባበል
እነኚህ መጽሐፍ ቢተረጉሙ፣ ሕግን ቢተነትኑ በዕውቀት የበለጸጉ ቢሆኑ የሚተረጉሙት የመጽሐፍ ቃል የሚተነትኑት ሕግ
እንዲሁም ገንዘብ ያደረጉት እውቀታቸው የምስራቹን ዜና እንዲመለከቱና እንዲሰሙ አላደረጋቸውም ይልቁንም ለያቸው
እንጂ፡፡ ዛሬም መምህራን ነን አዋቂዎች ነን ከኛ በላይ ለአሳር የሚሉ በንባብ የተተከሉ በትርጓሜ ያልፋፉና
ያልበለጸጉ የመንደር አውደልዳዮች ሳይተከሉ የተነቀሉ መምራን ባዮች ኋላ ከምስራቹ ዜና የመለየታቸው ከክብር
መጉደላቸውን ያመላክታል፡፡
✔ከሠይፍ አቀባበል
ሕይወት ለመስጠት የተወለደ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተገለጠበትና በመጣበት ወቅት ሰዎችን
በመግደልና ደም በማፍሰስ መቀበል እጅግ የከፋ ኃጢአት ነው፡፡ ዛሬ በልደቱ ቀን እንደ ሄሮድስ ሰውን ገድለን ደም
ባናፈስም እንደ እረኞች ፣ እንደ ሰብአ ሰገል፣ እንደ እንስሳቱ አምላካችን በተወለደበት ቤተልሔም ምሳሌ በሆነችላት
በቤተክርስቲያን በሌሊት ተገኝተን ከማሕሌቱ፣ ከቅዳሴው ከምስጋናው ከክቡር ሥጋና ደሙ መሳተፍ ሲገባን በዚህ ባለፈ
አክብሮና አልቆ ፈጥሮ ማደሪያው አድርጎ ባነጸው ሰውነታችን ሌሊቱን ሁሉ እስከ ንጋት በዘፈን፣ በስካር፣ በመዳራትና
በዝሙት በዓሉን ማክበር ጥንት ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደና በተገለጠ ጊዜ ሄሮድስ እንዳደረገው
አቀባበሉን በሰይፍና በደም እንደመቀበል ይቆጠርብናልና ከዚህ አይነት አቀባበል ልንለይ ይገባናል፡፡
እኛስ እንዴት ባለ አቀባበል በዓለ ልደቱን እናክብር?
ሰላም
ይእዜኒ ንትልዋ ለሰላም
እስመ ተወልደ ክርስቶስ ዮም በዛቲ ዕለት
ፍሥሐ ንዜኑ ለዘየአም ዜና ሠናየ ውእቱ ሕጻን
ኃይሎሙ ወፅንዖሙ ለእስራኤል