የሻንቆ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ተመረቀ

እንኳን ደስ አላችሁ!
እነሆ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የሻንቆ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ህዳር 6 ቀን 2011 ዓ.ም በሶስት ሊቃነ ጳጳሳት ቡራኬ ማለት በብጹዕ አቡነ ዕንባቆም በቅድስት ሀገረ ኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ገዳማት ሊቀጳጳስ በብጹዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ የጉራጌ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፊሊጶስ የደቡብ ኦሞ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ ተባርኮ ተመርቋል፡፡

በዕለቱ 315 አዳዲስ ተጠማቂያን ወደ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የተቀላቀሉ ሲሆን በቃለ እግዚአብሔርም ያመኑት እንዲጸኑ ተደርጓል፡፡

ከዚህም ጋር ተያይዞ በሐመር ወረዳ በቡስካ ታሪካዊ ተራራ ላይ ተገኝተው እኝሁ አባቶች የጽዮን ማርያም እና በቅዱስ አቡነ ሙሴ ጸሊም የተሰየመ ወደ ፊት ገዳም ባርከው የመሰረት ድንጋይ አስቀምጠዋል፡፡ይህ ስፍራ ለብዙ ዘመን በሐመር ህዝቦች ቅዱስ ስፍራ እንደሆነ እና የመላእክት ዝማሬ እንደሚሰሙበት የዕጣን ሽታ ሁሌ እንደማይታጣበት እንዲሁም የከበሮም ድምጽ እንደሚሰሙበት ደጋግመው ሲናገሩለት የነበር በደን የተሸፈነ ተራራ ነው፡፡

ከዚህም ጋር ተያይዞ ጅንካ በተመለሱበት ወቅት በደቡብ ኦሞ ሀገረ ስብከት ኮሚቴ አማካኝነት እየለማ ያለው ሰፊ የሙዝ እና የቲማቲም እርሻ ፕሮጀክት ጎብኝተዋል፡፡በኮሚቴ ከዚህ በፊት ተገዝቶ በተለገሰው የእርሻ ትራክተር እና የውሃ ፓንፕ እየለማ ያለው ሰፊ የሙዝ ምርትና የቲማቲም ምርት ቅድስት ቤተክርስቲያን የልማት ቤት መሆኗንና መስራት እንደምትችን ያስመሰከረ ፕሮጀክት ነው፡፡

የልማት ፕሮጀክቱ ፕሮጀክት አስተባባሪ እና የንዑስ ኮሚቴው ሰብሰባቢ አቶ ተኮላ ከተማ በዕለቱ ሲናገር ይህ ስራ በሌሎች ዘንድ ቤተክርስቲያን መሬት ትይዛለች እንጅ አታለማም የተባለው ክፉ ንግርት የሰበረ ስለሆነ ከሚገኘው ምርት በላይ ይህ ያኮራናል ሲል ገልጸዋል፡፡