እንኳን አደረሰን ፤ አደረሳችሁ! እንኳን ደስ አላችሁ!!

የጂንካ ቅድስት በአታ ለማርያም እና ቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያን የግንባታ ሥራው እንዲህ በአማረ መልኩ ተጠናቅቆ  ዛሬ የካቲት 8/2012 ዓ.ም

  1. ብጹዕ አቡነ ፊሊጶስ የደቡብ ኦሞ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስና የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩኒቨርሲቲ የበላይ ሊቀ ጳጳስ
  2. ብጹዕ አቡነ ናትናኤል የወለጋ ሁሩጉዱሩ አህጉረ ስብከት ሊቀጳጳስ
  3. ብጹዕ አቡነ ማቴዎስ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ የሚዲያ የበላይ ሊቀጳጳስ የጠቅላይ ቤተክህነት የስብከተ ወንጌል መምሪያ ሊቀጳጳስ
  4. ብጹዕ አቡነ አረጋዊ የጠቅላይ ቤተክርህነት የውጭ ጉዳይ መምሪያ ሊቀጳጳስ እንዲሁም የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በታላቅ ድምቀት ተመርቋል፡፡

ይህንን የመሰለ ውብ ቤተክርስቲያን ለመስራት ገንዘቡን ጉልበቱን እና ጊዜውን ለመስጠት ያልሰሰተ የጅንካ ህዝበ ክርስቲያን ሊመሰገን ይገባዋል፡፡የደቡብ ኦሞ ሀገረ ስብከት ስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ ልማትና ህንጻ ቤተክርስቲያን አሰሪ ኮሚቴ ምንም ትኩረቱ በገጠሪቱ የደቡብ ኦሞ ሀገረ ስብከት ቢሆን በህንጻ አሰሪ ኮሚቴው በተጠየቀው ድጋፍ መሰረት የበኩሉን በማድረግ ከቅድስት በአታ በረከት በመሳተፉ ደስታ ይሰማዋል፡፡

ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን!

የጉዞ ማስታወቂያ

የደቡብ ኦሞ ሀገረ ስብከት ኮሚቴ በየዓመቱ ከየካቲት 14-20/2012 የሚያደረገው ጉዞ ዘንድሮም በሚያምር ሁኔታ ለማድረግ ዝግጅቱን እያጠናቀቀ ነው፡፡

በጉዞዋችን የኦሞን ወንዝ ተሻግረን ኬንያ ድንበር ላይ ቃለ እግዚአብሔር ይሰበካል፡፡ቡስካ ተራራ  ላይ በኢትዮጵያ ውስጥ በስሙ በብቸኝነት የሚገነባው ታላቅና ድንቅ የቅዱስ አቡነ ሙሴ ጸሊም ገዳም በቡስካ ተራራ ላይ ይጎበኛል፡፡

ቱርካና ሀይቅ ዳር የሚገኙ የዳሰነች ብሄረሰብ፣ የሐመር፣ የበና፣ የማሌ፣ የሙርሲ፣ ብሔረሰቦችን ጨምሮ 12 አብያተክርስቲያናት ይጎበኛሉ፡፡

የበረሃ ማር እያበላ ቆዳ ለብሶ በበረ የኖረው መጥምቀ መለኮት በትክክለኛው ቦታ በበረሃ በሐመር በሸዳ በክብር ይጎበኛል፡፡

ኑ እኛም ጥምቀትና ቤተክርስቲያን እንፈልጋለን እያሉ ዘወትር የሚማጸኑ ወገኞቻችንን እንደግፋቸው፡፡

የጉዞ መነሻ ቀን የካቲት 14//2012

መመለሻ ፡- የካቲት 20/2012 ዓ.ም

መነሻ ቦታ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት

ስልክ 0961260126

ጌታችን በተወለደ ጊዜ የተፈጸሙ የአቀባበል ዓይነቶች

በዲ/ን አውራሪስ በላይ

ተወልደ ኢየሱስ በቤተልሔም ዘይሁዳ
አዋልደ ጢሮስ አሜሃ ይሰግዳ
ሰብአ ሰገል አምጽኡ ሎቱ ጋዳ
ወይተኃሠያ አዋልደ ይሁዳ

✟✟ እንኳን ለጌታችን ለአምላካችን ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት በሠላም አደረሳችሁ አደረሰን፡፡✟✟

ቤተ ክርስቲያናችን ከምታከብራቸው ዘጠኙ ዐበይት የጌታ በዓላት አንዱ ከሦስቱ አካል አንዱ አካል እግዚአብሔር ወልድ በርሱ ፈቃድ በአባቱ ፈቃድና በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ በብስራተ መልአክ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም በከብቶች በረት ለዓለም መድኃኒት ሊሆን በቤተልሔም የተወሰደበትን በዓለ ልደት ነው፡፡

✔የጌታችን ሰው ሆኖ መገለጡ

✥ ነበያት ውረድ ተወለድ ብለው ፤
✥ አበው በተስፋ ጽድቅህን ብርሃንን ኃይልን ላክልን ብለው የጮኹበት፣
✥ የአዳም ጸሎቱ ፍሬ ያገኘበት፣
✥ ሰው አምላክ አምላክ ሰው የሆነበት፣
✥ ሰውና መላእክት ሰውና እግዚአብሔር ሰማይና ምድር ህዝብና አሕዛብ የታረቁበት፣
✥ የክርስትና ሃይማኖት የመገለጥ ሃይማኖት መሆኗ የተመሠከረበበት
✥ እንዲሁም ሊቁ ሱኑቲዮ እንደተናገረው “ልደት ቀዳማዊ ተዐወቀ በልደት ደኃራዊ ” እንዳለ ቅድመ ዓለም ከአብ ያለ እናት መወለዱ ድኅረ ዓለም ከእናት ያለ አባት በመወለዱ የታወቀበት ዐቢይ በዓል ነው፡፡

ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆነ በሥጋ ማርያም ተገልጦ በቤተልሔም በተወለደ ጊዜ በወቅቱ የነበረውን አቀባበል በአምስት ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡

1. የትጉሃን አቀባበል
2. የእንቅልፋሞች አቀባበል
3. የንፉጋን አቀባበል
4. የደንታቢሶች አቀባበል
5. የሠይፍ አቀባበል ናቸው፡፡

1. የትጉሃን አቀባበል

1.1የትጉሃን መላእክት አቀባበል

በዕለተ እሑድ የተፈጠሩ መላዕክት አምላክ ወልደ አምላክ የሆነ ጌታችን በተወለደ ጊዜ ነቅተውና ተግተው በቤተልሔም ዙሪያ ተሰብስበው በምስጋና ተቀብለውታል፡፡ ከዚያም አልፎ የምስራቹን ለዓለም ተናግረዋል፣የመላአክትን ምስጋና በተመለከተ ቅ/ያሬድ በአንቀጸ ብርሃኑ ሲገልጠው “ልጅሽንም በዚህ አለም በወለድሽው ጊዜ ዓይኖቻቸው ብዙዎች የሆኑ ኪሩቤልና ክፍፎቻቸው ስድስት የሆኑ ሱራፌል በበረት ውስጥጋረዱሽ የብርሃን ደመናዎችም ከበቡሽ የመለአክት አለቆች የመላእክት ሠራዊትና የሰማይ ጭፍሮች በመፍራትና በመንቀጥቀጥ በፊትሽ ቆሙ በዚህም ዓለም ኪሩቤልና ሱራፌል በሰማያት ካለው ምስጋናቸው ወይም ከቀድሞ ምስጋናቸው ወገን ባልሆነ በሌላ /አዲስ/ ምስጋና አመሰገኑሽ ፍጥረትን ሁሉ ሰብስቦ የያዘና ፍጥረቱን ሁሉ የሚመግብ ጌታቸው በብብትሽ /በክንድሽ/ ተቀምጦ ጡትሽን እንደ ህጻን ሲጠባ ባዩ ጊዜ በአርያም ፈለጉና በዚህ ዓለም እንደቀድሞው ከአባቱና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር አገኙት የጌታ ትሕትናውን ባዩ ጊዜም ዓይኖቻቸውን ወደ ላይ ወደ አርያም ከፍ ከፍ አደረጉ ክንፋቸውንም ዘርግተው ለሁሉ ጌታ ለአንተ ምስጋና ይገባል እያሉ ጌታቸውን አመሰገኑ ዳግመኛም በዋሻ በጎል ውስጥ አንቺን ከሕጻንሽ ጋር አይተው በምድር ላይ ሠላም ፍቅር አንድነት ሆነ አሉ” ብሎ አቀባበላቸውን ገልጾልናል፡፡

1.2 የትጉሃን እረኞች አቀባበል

በሉቃ 2፥8-20 እንደተገለጠው በሌሊት መንጋቸውን ይጠብቁ ለነበሩ እረኞች የእግዚአብሔር መልአክ ተገልጦላቸው የምስራቹን ዜና በነገራቸው ጊዜ ይህን በጆሯቸው የሰሙትን በዓይናቸው ለማየትና ለማመስገን ተግተው ከእረኝነት ተግባራቸው በመነሣት ወደ ቤተልሔም በመገስገስ ምስጋና አቅርበውና ሰግደው ከመላእክት ጋር በአንድነት በማመስገናቸው ቀድሞ በመጽሐፍ እንደተነገረ “ዮም አሐደ መርዔተ ከኑ መላእክት ወሰብእ ከመይስብሕዎ ለክርስቶስ በቃለ አሚን” የተባለው መጽሐፋዊ ቃል ተፈጸመ ዳግመኛም “የአዳም ምስጋና ከመላእክት ምስጋና ጋር አንድ ሆነ ምስጋናቸውም የተስተካከለ ሆነ ተብሎ የተነገረው ቃል ተረጋገጠ” 3ኛመቃ 4፥11 በዚህም የእረኞቹ ተግቶ መቀበልና በተወለደበት ስፍራ መገኘት የመጽሐፍ ቃል እንዲፈጸም አደረጉ የልደቱ እማኞችም ሆኑ፡፡

1.3 የእንስሳት አቀባበል

ቅ.ል.ከ ከ700 ዓመት በፊት ኢሳይያስ በትንቢቱ “በሬ ገዢውን አህያም የጌታውን ጋጣ አወቀ፤ እስራኤል ግን አላወቀም ሕዝቡም አላስተዋለም ” ት.ኢሣ 1፥3 ብሎ እንደተናገረው ጌታችን አምላካችን በተወለደ ጊዜ ወራቱ ብርድ የጸናበት እመቤታችንም ትጠቀልልበት ዘንድ መጠቅለያና ጨርቅ ያጣችበት በነበረ ሰዓት እንስሳት አህያ በሬ ላም ቢል ወገኑ አንድ ነውና ጌታቸው መሆኑን አውቀው የሰጣቸውን እስትንፋስ ስጦታ አድርገው በመስጠት በልደቱ ተካፋይ ሆነዋል እስትንፋስ በመለገስ መልካም አቀባበልም አድርገውለታል፡፡

1.4 የሰብአ ሰገል አቀባበል

ከ1000 ዓመት በፊት ልበ አምላክ ዳዊት “የተርሴስ ደሴቶችና ነገሥታት ስጦታ ያመጣሉ የአረብና የሳባ ነገሥታት እጅ መንሻ ያቀርባሉ ነገሥታት ሁሉ ይሰግዱለታል አሕዛብም ይገዙለታል ” መዝ 71፤10-11 እንዳለ ሦስቱ ነገሥታት ማንቱሲማር፣ ዲዲያስፋና ሜልኮስ የአባታቸውን የዘረድሸትን ቃል ሰምተውና የነገራቸውም ሲፈጸም ሦስቱም እያንዳንዳቸው 10 ሺህ ሰራዊት አስከትለው ከሩቅ አገር በመምጣት ወርቅ እጣን ከርቤ እጅ መንሻ ገብረው በፊቱም ወድቀው ሰግደው አቀባበል አድርገውለታል፡፡ማቴ 2፥1-13

2. የእንቅልፋሞች አቀባበል

ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም በቤተልሔም ሲወለድ ሌሊት እንደነበር ወንጌል ይነግረናል /ሉቃ2፥8-20/ ይህንን አስቀድሞ ትንቢት የተነገረላቸው ሱባኤ የተቆጠረላቸው የአበውን ተስፋ ሲጠባበቁ የነበሩ በቅርብ ያሉ ሕዝበ እስራኤል ግን በዚህ የመዳን ቀንና የምስራቹ ዜና በዓለም በታወጀበት ጊዜአንቀላፍተው በመገኘታቸው ክብሩን ግርማውን እንዳያዩና የሩቅ ሀገር ሰዎች ቀድመው ተግተው በመገኘት ትንቢተ ነቢያት ሲፈጸም ተስፋ አበው ሲበሰር ከምስራቹ እንዲሳተፉ ሆነዋል፡፡ ለዚህም ነው ቅዱስ ዮሐንስ በወንጌሉ ሲገልጽ እስራኤል ለዚህ ለበዓለ ልደቱ ለምስራቹ ዜና ስላልበቁና ለማየትም ስላልታደሉ ወገኔ ብሎ ወደ እነርሱ ሲመጣ ላለመቀበል የወሰኑትና እስከ መስቀል ሞትም ያደረሱት ዮሐ1፥11

3. የንፉጋን አቀባበል

እመቤታችን ልጇን አምላካችንን ክርስቶስን ልትወልድ ባለች ጊዜ አውግስጦስ ቄሳር የተባለ ሃገረ ገዢ ሕዝብ ሁሉ እንዲቆጠር አዋጅ አውጆ ነበር ሉቃ 2፥1 በዚህም በቤተልሔምና ዙሪያ ብዙ ሕዝብ ተሰብስቦ ማረፊያም ይዘው ነበር እመቤታችንም በዚያ ሳለች በመውለጃዋ ሰዓት ሲደርስ አረጋዊ ዮሴፍ ማሳደሪያ እንዲሰጡት ሁሉን ቢጠይቅ እምቢ አሉ አኃዜ ዓለም በእዴሁ የተባለ አምላክ የሚወለድበት ስፍራ አጥቶ ደጃፉን የሚከፍትለት ሰው አጥቶ የከብቶች በረት ተወለደ በዚህም ክብር ከሰዎች ርቃ ለእንስሳት ሆነ፡፡

4. የደንታ ቢሶች አቀባበል

ይህ አይነቱ አቀባበል የካሕናተ አይሁድ አቀባበል ነው እነዚህ በህዝብ ላይ ለማስተማርና ለመፍረድ የተሾሙ የኦሪትና የነብያትን መጽሐፍት ጠንቅቀው የሚያውቁና ምስክር የሆኑ የሕዝብ መሪዎች የሚያውቁትን የሚተረጉሙትን ሕግ ሳይጠቅማቸው ቀድሞውንም መጽሐፍ እንዳለ ዓላማቸው በክብር በስልጣን በመዐረግ ሰበብ የሕዝቡን ገንዘብ በመቀበል መክበር ነበርና ይከብሩበትና ይመሰገኑበት የነበረውን አምላክ ሳይቀበሉት ከምስክርነቱና ከምስራቹ ሕይወት ፊት የራቁና የተለዩ ሆኑ፡፡ማቴ 23፥14

5. የሠይፍ አቀባበል

ይህ አይነቱ አቀባበል የንጉሥ ሄሮድስ አቀባበል ነው፣፣ ከሩቅ አገር የመጡ ሰብአ ሰገል /የጥበብ ሰዎች/ ኮከብ እየመራች አምጥታ ስትሰወርባቸው ንጉሥ ሁሉን ያውቃል ብለው ሄሮድስን ከዓለም አስቀድሞ ንጉሥ የሆነውን ክርስቶስን በየት እንደተወለደ በጠየቁት ጊዜ ጉልበቱ ርዶ ልቡ ደንዝዞ ቀርቶ ነበር ይሁንና ረበናተ አይሁድን ጠርቶ መልስ አግኝቶ ሰብአ ሰገልም ጠይቆ ዓመቱን ከተረዳ በኋላ ሄደው አንዲሰግዱና እርሱም ለሰገደለት ወደ ርሱ እንዲያመጡ ጠይቆ ነበር ይሁንና መልአከ እግዚአብሔር ሰብአ ሰገል ከቤተልሔም ተገኘው ከልደቱ ምስራች ተሳታፊ ከሆኑ በኋላ በሌላ መንገድ እንዲሄዱ ነግሯቸው ነበርና ሄደው ቢያጣቸዉ 144,000 ሕጻናትን ክርስቶስን እገድላለሁ ብሎ ደም አፍስሶ አስፈጃቸው እንዲህ ባለ አቀባበል ለዓለም መድኅን ለቤዛ ዓለም የመጣን ክርስቶስን እንዲህ ባለ አቀባበል ተቀበለ፡፡

✔ከአቀባበሎቹ ምን እንማራለን

ከትጉሃን ተቀባዮች ስንመለከት በተለይ የእረኞች የሰብአ ሰገልና የእንስሳት አቀባበል ብዙ ነገር ያስተምረናል

❖ ከእንስሳት፡-

አላዋቂ ሆነው የተፈጠሩ እንስሳት ጌታችን በተወለደ ጊዜ ቤተልሔም+— እንደነበረች ተረድተው ሲፈጥራቸው የሰጣቸውን ትንፋሻቸውን በመለገስ እንዳሟሟቁት እኛም አዋቂ ሆነን የተፈጠርን እርሱ እግዚአብሔር ወደ ፈቀደ ከሰጠን ሀብት፤እውቀት፣ጉልበትና ጊዜን ለሰጠን ለእግዚአብሔር አምላክ መስጠት እና የሰጠህኝን ሰጠውህ ልንል ይገባል፡፡

❖ ከእረኞች፡-

እረኞች የተናቁ የተዋረደ ስራ ሰርተው የሚኖሩ ቢሆንም ኃላፊነታቸውን ባለመዘንጋት የሰሙትን የምስራች ቃል አይተው ከምስጋናው ለመሳተፍ ወደ ቤተልሔም እንደገሰግሱ እኛም ም ቤተልሔም ተብላ በምትጠራ በበቤተክርስቲያን የምስራቹን ወንጌል ለመስማት እና በቤተልሔም የተገኘውን ጌታችንና እመቤታችንን እንዲሁም እንደ ቅዱሳኑ አረጋዊ ዮሴፍና ሰሎሜን ለማመስገን ፈጥነን ገስግሰን ወደ ቤተ ክርስቲያን ልንመጣ ይገባል፡፡

❖ ከሰብአ ሰገል፡-

እነኚህ የምድር ነገሥታት ናቸው ሀገር የሚያስተዳድሩ ፤ሕዝብ የሚመሩና በሠራዊት የሚታጀቡ ናቸው፡፡ ነገር ግን ይህ ሁሉ ክብር ይህ ሁሉ ስልጣን እሾህ /ማነቆ/ ሳይሆናቸው አምላክነቱን ንጉሥነቱን አዳኝነቱን አውቀው እጅ መንሻ ይዘው እንደመጡ ገዢነታችን ክብራችን ሳያሸንፈን ለምስጋና ለአበርክቶት ወደ እናትና ልጅ እንዲሁም ቅዱሳኑ ወደሚገኙበት ወደ ቤተክርስቲያን ልንመጣ ይገባል፡፡

❖ ሰብአ ሰገል ቤተልሔም በደረሱ ጊዜ ጌታ የተወለደው ጭቃ በበዛበት የከብቶች እዳሪ እበት ያጨማለቀው ቢሆንም ስፍራውን ሳይንቁ ወደው አጎንብሰው በመስገድ አንዳመሰገኑና እጅ መንሻ እንዳቀበሉ እኛም ቤተልሔም የተባለች ቤተክርስቲያንን ስንወድንና ለአኮቴት ለአምልኮ ስንመጣ ከነ ችግሯ መከራዋና ፈተናዎቿ ሁሉ መሆን ይገባል፡፡

✔ከእንቅልፋሞች አቀባበል

እነዚህ ትንቢት ተነግሮላቸዉ ሱባኤም ተቆጥሮላቸው ከቤተልሔም ቅርብ ሆነው ሳለ በስንፍናቸው ምክንያት ከምስራቹ ዜና ተለይተዋል፤ እኛም በሃይማኖት ጸንተን ከቤተክርስቲያን ቀርበን ሳለ በዝንጋኤና ስንፍና ከተሰበከችልንና ከምትሰበክልን ከምስራቿ የወንጌል ቃለ ትምህርት ርቀን ሩቅ የተባሉት ከሃዲያን መናፍቃን አሕዛብ ለምስክርነትና ለክብር ለምስጋና እንዳይቀድሙን ተግተንና ነቅተን በቤተልሔም ቤተክርስቲያን ቀድመን ልንገኝና ምስክር ልንሆን ይገባናል

✔ከንፉጋን አቀባባል

እነኚህ ሰዎች በከተማቸው በመኖሪያ መንደራቸው ሊደረግላቸው የታሰበውን ታላቅ ብስራት በራስ ወዳድነታቸውና ተቀባይና አክባሪ ባለመሆናቸው አምላክችን ከእመቤታችን ጋር እንዲሁም ከቅዱሳኑ አረጋዊ ዮሴፍና ሰሎሜ ጋር ሲመጣ ላለመቀበል በመወሰናቸው ሳይቀበሉ በራቸውን ዘግተው ተገኙ፡፡ ዛሬም የእውነት አምላክ የሆነ የክርስቶስን አምላክነት፣ አዳኝነት፣ እግዚአብሔርነት አምኖ ላለመቀበል፣ የወላዲተ አምላክን እናትነት አማላጅነትና ቃል ኪዳንነት ላለማመን በቅዱሳንን ተራዳኢነትና አማላጅነት ላለመማጸን በመወሰን ማደሪያ የተባለ ልባቸውን የሚዘጉና ፍቃደኛ ላልሆኑ አማኞች ኋላ ኋላ የእግዚአብሔር ክብር ርቃቸው ከእነርሱም ተለይታ በሃይማኖት ጎዶሎነት በምግባር ብሉሽነት እንስሶች ምሣሌ የሆኑላቸው ከሃዲያን መናፍቃን አሕዛብ ይከብሩባታል ይመሰገኑባታል ማለት ነው፡፡

✔ከደንታ ቢሶች አቀባበል

እነኚህ መጽሐፍ ቢተረጉሙ፣ ሕግን ቢተነትኑ በዕውቀት የበለጸጉ ቢሆኑ የሚተረጉሙት የመጽሐፍ ቃል የሚተነትኑት ሕግ እንዲሁም ገንዘብ ያደረጉት እውቀታቸው የምስራቹን ዜና እንዲመለከቱና እንዲሰሙ አላደረጋቸውም ይልቁንም ለያቸው እንጂ፡፡ ዛሬም መምህራን ነን አዋቂዎች ነን ከኛ በላይ ለአሳር የሚሉ በንባብ የተተከሉ በትርጓሜ ያልፋፉና ያልበለጸጉ የመንደር አውደልዳዮች ሳይተከሉ የተነቀሉ መምራን ባዮች ኋላ ከምስራቹ ዜና የመለየታቸው ከክብር መጉደላቸውን ያመላክታል፡፡

✔ከሠይፍ አቀባበል

ሕይወት ለመስጠት የተወለደ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተገለጠበትና በመጣበት ወቅት ሰዎችን በመግደልና ደም በማፍሰስ መቀበል እጅግ የከፋ ኃጢአት ነው፡፡ ዛሬ በልደቱ ቀን እንደ ሄሮድስ ሰውን ገድለን ደም ባናፈስም እንደ እረኞች ፣ እንደ ሰብአ ሰገል፣ እንደ እንስሳቱ አምላካችን በተወለደበት ቤተልሔም ምሳሌ በሆነችላት በቤተክርስቲያን በሌሊት ተገኝተን ከማሕሌቱ፣ ከቅዳሴው ከምስጋናው ከክቡር ሥጋና ደሙ መሳተፍ ሲገባን በዚህ ባለፈ አክብሮና አልቆ ፈጥሮ ማደሪያው አድርጎ ባነጸው ሰውነታችን ሌሊቱን ሁሉ እስከ ንጋት በዘፈን፣ በስካር፣ በመዳራትና በዝሙት በዓሉን ማክበር ጥንት ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደና በተገለጠ ጊዜ ሄሮድስ እንዳደረገው አቀባበሉን በሰይፍና በደም እንደመቀበል ይቆጠርብናልና ከዚህ አይነት አቀባበል ልንለይ ይገባናል፡፡

እኛስ እንዴት ባለ አቀባበል በዓለ ልደቱን እናክብር?

ሰላም
ይእዜኒ ንትልዋ ለሰላም
እስመ ተወልደ ክርስቶስ ዮም በዛቲ ዕለት
ፍሥሐ ንዜኑ ለዘየአም ዜና ሠናየ ውእቱ ሕጻን
ኃይሎሙ ወፅንዖሙ ለእስራኤል

እናስታውስዎ

የደቡብ ኦሞ ኮሚቴ ከሚያከናውናቸው ሁለት ዐበይት ጉዞዎች መካከል በየዓመቱ የካቲት 15-22/2012 የሚደረገው ጎዞ አንዱ ነው፡፡

ከቦታው አስቸጋሪነት የተነሳ ኮሚቴው ይዞ የሚሄደው አንድ መኪና ብቻ መሆኑን ከወዲሁ እያሳወቅን መጓዝ የምትፈልጉ አባላትና ደጋፊዎቻችን የቀሩን ቦታዎች ውስን ስለሆኑና ለጉዞ የቀረው ሁለት ወር ብቻ በመሆኑ ከወዲሁ እንድትመዘገቡ ለማሳሰብ እንወዳለን፡፡

የደቡብ ኦሞ ኮሚቴ

የጉዞ ንኡስ ክፍል  

ዜና ቤተ ክርስቲያን

የጥምቀት በዓል በዓለም ከማይዳሰሱ ቅርሶች መዝገብ ውስጥ ተካተተ ::
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሳይንስ ፣ ትምህርትና ባህል ተቋም (ዩኔስኮ) የአገራት ቅርስ መመዝገብ ኮሚቴ ኮሎምቢያ ቦኮታ፤ ባደረገው ስብሰባ ነው የጥምቀት በዓል በዓለም ከማይዳሰሱ ቅርሶች መካከል እንዲካተት የወሰነው። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከዚህ ቀደም የመስቀል በዓልን በአለም ከማይዳሰሱ ቅርሶች መዝገብ ውስጥ ማስፈሯ ይታወሳል። ዮኔስኮ የሚመዘግባቸው ቅርሶች ለቱሪዝም እድገትም ከፍተኛ ድርሻ እንደሚኖራቸው ይታወቃል።

እንኳን አደረሳችሁ !!

እንኳን ለልዑል አባታችን ለቅዱስ አማኑኤል ዓመታዊ በአል በሰላምና በጤና አደረሳችሁ

ወደ ደቡብ ኦሞ ተጉዛችሁ እኝህን 16 ብሔረሰቦችን ለማየትና በአካል የተሰሩ አብያተክርስቲያናትን ለመጎብኘት ኬንያ ጠረፍ የምትገኘውን ቅድስት ኪዳነ ምህረት ለመሳለም የምትፈልጉ የየካቲት ጉዞ ምዝገባ ተጀምሯል፡፡ ለመመዝገብ ለምትፈልጉ ሰሞኑን አውደ ርእይ በሚታይበት በላፍቶ ደብረ ኢያሪኮ መድኃኒዓለም ቤተክርስቲያን በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አንደኛ ፎቅ ቢሮ ቁጥር 121

ስልክ ፡-0961260126/0916583034

ደቡብ አሞ ኮሚቴ

አውደ ርእይው ተከፈተ

በላፍቶ ደብረ ኢያሪኮ መድኃኒዓለም ቤተክርስቲያን የዘጋጀው አውደ ርእይ ዛሬ በዋዜማው ጥቅምት 26/2/2012ዓ.ም በታላቅ ድምቀት ተከፍቷል።
አውደ ርእይው በቤተክርቲያኑ አስተዳደር መላከ ሰላም መምህር በቃሉ እና በመላው የሰበካ ጉባኤው አባላት ግብዣ የተዘጋጀ ነው።
አውደ ርእይ የተዘጋጀው በላፍቶና አከባቢው ያሉ ምእመናን ሁሉ በበቂ ሁኔታ መረዳትና መመልከት እንዲችሉ እስከ መጪው ዕሁድ ጥቅምት 30/2/2012ዓ.ም ድረስ ለአምስት ቀን የሚቆይ ይሆናል።
በመሆኑ በበአሉና ዋዜማው መመልከት ያልቻላችሁ ምእመናን ቅዳሜና ዕሁድ እንድትጠቀሙ እንድትመለከቱ እንጋብዛለን።
በደብረ ኢያሪኮ እና አካባቢው የምትገኙ ኦርቶዶክሳዊያን በሙሉ ኑ በእግዚአብሔር ደስ ይበላችሁ
የደቡብ ኦሞ ኮሚቴ

The gallery was not found!

በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5 ቁጥር 164 ድንጋጌ መሠረት ከጥቅምት 12 እስከ ጥቅምት 24 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ የተካሄደውን የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ አስመልከቶ ከቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ፤

1. ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የመክፈቻ ንግግር ሆኖ ለምልዓተ ጉባኤው የቀረበው መልእክት በቀጣይ በቤተ ክርስቲያናችን ለሚከናወነው መንፈሳዊውም ሆነ ማህበራዊ ተልዕኮ ጠቃሚነቱ የጐላ በመሆኑ ጉባኤው የሥራ መመሪያ አድርጐ ተቀብሎታል፡፡
2. የሀገር ሰላምን ጉዳይ አስመልክቶ በአሁኑ ጊዜ በአገራችን ኢትዮጵያ እየታየ ያለው የሰው ሕይወት መጥፋትና የዜጎች ንብረት መውደም፣ ቅዱስ ሲኖዶሱን በእጅጉ ያሳዘነ ሲሆን፣ መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ ሰላምን እንዲያስከብር፣ የዜጎች ደህንነት እንዲጠበቅ እንዲያደርግ፣ የተፈናቀሉትም ወደቀያቸው እንዲመለሱና ለጠፋው ንብረታቸው ማቋቋሚያ እንዲደረግላቸው፣ በተለይም በክርስቲያኖችና በአብያተ ክርስቲያናት ላይ እየደረሰ ያለው ስደትና መከራ ጐልቶ እየታየ በመሆኑ የጥፋቱ መልእክተኞችን መንግሥት በሕግ እንዲጠየቁ እንዲያደርግ ቅዱስ ሲኖዶስ እያሳሰበ መንግሥትም ለሕዝቡ ብርቱ የበኩሉን ጥበቃ እንዲያደርግ፣
3. በቤተ ክርስቲያናችን የሚከናወነውን መንፈሳዊም ይሁን ማህበራዊ ተግባራት በአግባቡ ማስተላለፍ እንዲቻል የቤተ ክርስቲያኒቱ የሕዝብ ግንኙነት በመምሪያ ደረጃ እንዲቋቋም፣
4. በአገራችን በተለያዩ ክልሎች የተለያዩ ቋንቋ ተናጋሪዎች በብዛት እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም የቤተ ክርስቲያኒቱን ተከታዮች በቋንቋቸው ማስተማርና ማገልገል እንዲቻል በየአህጉረ ስብከቶቹ የሚገኙ የአብነት ት/ቤቶችን ማጠናከር ከልዩ ልዩ ቋንቋ ተናጋሪዎች አገልጋዮችን ማፍራት እንዲቻል ለት/ቤቶቹ ማጠናከሪያ የሚሆን ቋሚ በጀት እንዲመደብ፣ በቀጣይም በሁሉም አፍ መፍቻ ቋንቋ በማዕከል ማሠልጠኛ እንዲቋቋም፤
5. የአገራችን ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በአገራችንና በአፍሪካ ጭምር ያበረከቱት የሰላም ተልዕኮ አስመልክቶ ዓለም አቀፍ የኖቤል ተሸላሚ መሆናቸው፣ በተለይም ለአገራችን ኢትዮጵያ ከፍተኛ እውቅና ያስገኘላት ቀድሞም የነበረ ክብሯን አጉልቶ ያሳየ በመሆኑ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ አድናቆቱን ገልጿል፡፡ ለወደፊቱም ለአገራችን እድገትና ብልጽግና በመንግሥት በኩል ለሚሠራው ማህበራዊና ልማታዊ ሥራ ቤተ ክርስቲያናችን አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ትቀጥላለች፡፡
6. አገራችን ኢትዮጵያ በጀመረችው የልማት አቅጣጫ በስፋት ለማስቀጠልና በተለይም ዜጎችን ከድህነት ለማላቀቅ በእጅጉ ተስፋ የተጣለበት የዓባይ ግድብ በተያዘው የግንባታ ሥራ ተፋጥኖ ግድቡ እንዲጠናቀቅና ሥራ እንዲጀምር ለማስቻል መላው የአገራችን ሕዝቦች አስፈላጊውን ዕገዛ በማድረግ እንዲቀጥሉ ቅዱስ ሲኖዶስ ያሳስባል፡፡
7. የቤተ ክርስቲያናችንን አጠቃላይ መሪ እቅድ በተመለከተ ቀደም ሲል በቅዱስ ሲኖዶስ በተወሰነው መሠረት በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ በኩል ወደተግባር እየተገባ መሆኑን ጉባኤው ከቀረበው ሪፖርት አዳምጧል፡፡ በቀጣይም ሥራው ተፋጥኖ እንዲቀጥልና ከካህናት ከምእመናን ከወጣቱም ጭምር የሚቀርቡ ወቅታዊ አቤቱታዎች በመሪ እቅዱ እየተጠኑ አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥ ተወስኗል፡፡
8. በግንቦቱ ርክበ ካህናት በቤተ ክርስቲያናችን የተቋቋመው አገራዊ የሰላምና የእርቅ ኮሚቴ የ4 ወራት ሪፖርት ለጉባኤው አቅርቧል፡፡ ኮሚቴውም ያከናወነው የሰላም ተልዕኮ ጉባኤው በአድናቆት ተቀብሎ በቀጣይም ኮሚቴው ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከምሁራንና ከወጣቶች የተውጣጡ አባላትን አካቶ የሰላምና የእርቅ ሥራውን አጠናክሮ እንዲቀጥል በማሳሰብ፣ ለዚህም የሚሆን አስፈላጊ በጀት መድቧል፡፡
9. በአገራችን በኢትዮጵያ በኦሮምያ ክልል በሚገኙ ወገኖቻችን ላይ በደረሰው የሰው ሕይወት መጥፋትና ስደት ላይ በመነጋገር በጣም ለተቸገሩ ወገኖች በጊዜያዊነት የሚደርስ ምግብና አልባሳት ለማቅረብ እንዲቻል አስፈላጊውን ገንዘብ እንዲመደብ፣ በቀጣይም በክልሉ ይህንን ችግር እየተከታተለ ዘለቄታዊ ርዳታ የሚያሰባስብ ኮሚቴ እንዲቋቋም ተወስኗል፡፡
10. የጌዴኦና ቡርጂ ዞኖች እስከአሁን ድረስ በሲዳማ ሀገረ ስብከት ሥር ሆነው መንፈሳዊውን አገልግሎት ሲያገኙና ሲተዳደሩ የቆየ ቢሆንም በአሁኑ ጊዜ ራሱን ችሎ ሀገረ ስብከት እንዲሆንላቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት ራሱን የቻለ ሀገረ ስብከት እንዲሆን ተወስኗል፡፡
11. በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እና በሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሞስኮ መንበረ ፓትርያርክ መካከል ሊኖር ስለሚገባው ግንኙነት በተመለከተ ከቤተ ክርስቲያናችን የውጭ ግኑኝነት መምሪያ በቀረበ ሪፖርት ላይ ጉባኤው ተነጋግሮ በሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት የነበረው ጥንታዊ ግንኙነት ወደፊትም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ተወስኗል፡፡
12. በስዊድን ሀገር ሶደርቴሌ ከተማን ማዕከል ያደረገ የቅዱስ አግናጥዮስ ኦርቶዶከስ ተዋሕዶ ሴሚናሪ በመላው አውሮፓ ለሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ምእመናን እና አገልጋይ ካህናት ስለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ጥንታዊ የአብነት ትምህርትና ዘመናዊ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ነገረ መለኮት ስልጠና የሚሰጥ ከፍተኛ የትምህርት ማዕከል በመሆኑ በቤተ ክርስቲያናችን ስም ዕውቅና እንዲያኝ ተወስኗል፡፡ አገልግሎቱን በስፋትና በብቃት እንዲያከናውን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስም የዕውቅና ደብዳቤ እንዲደርሰውም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ወስኗል፡፡
13. የ2012 ዓ.ም በጀት ዓመት የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ በጀት አስመልክቶ ከበጀትና ሂሣብ መምሪያ በቀረበው እቅድ ላይ በመነጋገር የቀረበው በጀት ላይ ማሻሻያ በማድረግ የ2012 ዓ.ም. በጀት በማጽደቅ በሥራ ላይ እንዲውል ተወስኗል፡፡
14. በአሁኑ ጊዜ በአገራችን በተለያዩ አካባቢዎች እየታየ ያለው ችግር እንዲያበቃ እግዚአብሔር አምላክ ምህረቱን እንዲሰጠን የተጀመረው ሱባኤ እንዲቀጥል ተወስኗል፡፡
ጥንታዊትና ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን ከጥንት ጀምሮ የአገር ባለውለታ እንደመሆኗ ሁሉ ወደፊትም በአገራችን ኢትዮጵያ በመንግሥትና በሕዝቡ ትብብር ለአገር አንድነትና ለዜጎች መብት መከበር፣ ለሰው ልጆች እኩልነት ለሚደረገው አገራዊ ጥረት የበኩሏን አስተዋጽኦ ከማድረግ አትቆጠብም፡፡
ሆኖም ለዚሁ አገራዊ ስኬት ከሁሉም በላይ በዜጎች መካከል መከባበርና ሰላማዊ አንድነት መኖር ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ መሆኑን ቅዱስ ሲኖዶስ ያምናል፡፡
ስለዚህ ኢትዮጵያውያን ልጆቻችን ሁሉ በአሁኑ ጊዜ ለአገራዊ አንድነታችን ሰላም ቅድሚያ የሚሰጠው መሆኑን አምናችሁ በአንድነት በሰላምና ተከባብሮ በጋራ ለመኖር፣ ለመሥራትም ሆነ ሠርቶ ለመበልፀግ አገራዊ አንድነታችሁን እንድታጠናክሩ ቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪውን ያቀርባል፡፡
የአገራችን መንግሥትም የአገር ሰላም፣ የዜጎች ደህንነትና በሰላም ወጥቶ መግባት ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር መሆኑን፣ ክቡር የሆነው የሰው ልጅ ሕይወት በምንም መልኩ በከንቱ መጥፋት የሌለበት መሆኑን ተገንዝቦ፣ ሰላምን የማስከበሩን፣ አገር የመጠበቁንና ዜጎችን በአገራቸው በእኩልነት ተሳስበው የሚኖሩበትን መንገድ በመቀየስ መንግሥታዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ቅዱስ ሲኖዶስ አጥብቆ ያሳስባል፡፡
በመጨረሻም ከጥቅምት 11 እስከ 24 ቀን ለ13 ቀናት በቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳዊና ማህበራዊ እንዲሁም አገራዊ ጉዳዮች ላይ ሲነጋገር የቆየው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በሰላም ተጠናቅቆ በዛሬው ቀን በጸሎት ተዘግቷል፡፡
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ
ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን!
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም
ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
ጥቅምት 24 ቀን 2012 ዓ.ም
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ
source; የኢኦተቤ መገናኛ ብዙኃን አገልግሎት ስርጭት ድርጅት/ EOTC Broadcasting Service Agency/

ታላቅ አውደ ርእይ በላፍቶ ደብረ ኢያሪኮ መድኃኒዓለም ቤተክርስቲያን

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!

እኛም ጥምቀትና ቤተክርስቲያን እንፈልጋለን!!

የደቡብ ኦሞ ሀገረ ስብከት ስብከተ ወንጌል ማስፋፊያና ልማት ህንጻ ቤተክርስቲያን አሰሪ ኮሚቴ በደብረ ኢያሪኮ መድኃኒዓለም ቤተክርስቲያን በሰበካ ጉባኤው መልካም ፈቃድ የመድኃኒዓለም ዓመታዊ በአልን ምክንያት በማድረግ ከዋዜማው ረቡዕ ጥቅምት 26/2012 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ዕሁድ ጥቅምት 30/2012 ዓ.ም ለአምስት ቀን  የሚቆይ ልዩ አውደ ርእይ አዘጋጅቶ ይጠብቃችኃል፡፡

ከዚህ በፊት ይህ ልዩ አውደ ርእይ ወደ እዚህ ቤተክርስቲያን ይዘን እንድንመጣ ስትጠይቁ የነበራችሁ የኮሚቴው አባላትና የዓላማው ደጋፊዎች በሙሉ እንኳን ደስ አላችሁ እያልን፡፡

በእነዚህ ቀናቶች እየተገኛችሁ እግዚአብሔር በደቡብ ኦሞ እያደረገልን ያለውን ድንቅ ነገር እንድትመለከቱ እና ስለሆነው ሁሉ ልዑል እግዚአብሔርን እድታመሰግኑ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡

የእግዚአብሔር ሰላም ከሁላችን ጋር ይሁን!!