አዳዲስ ምዕመናን ተጠመቁ

የደቡብ ኦሞ ሀገረ ስብከት ስብከት ወንጌል ማስፋፊያ ልማትና ህንጻ ቤተክርስቲያን አሰሪ ኮሚቴ በዳሰነች ወረዳ በነምረሙስ ቅድስት ኪዳነ ምህረትና በበሸዳ ቅዱስ ዮሐንስ ቤተክርስቲያ ባዘጋጀው የጥምቀት ፕሮግራም ላይ በነምረሙዝ 1537 በበሸዳ 117 አዲስ አማንያን በድምሩ 1654 ምዕመናን ወደዚህ ቤተክርስቲያን ህብረት ተቀላቅለዋል፡፡

ይህን የጥምቀት ፕሮግራም ኮሚቴው ያዘጋጀና ያስተባበረ ሲሆን ለተጠማቂዎቹ ቅድመ ጥምቀት ስልጠና እንዲሰጣቸው 18 ወጣቶች ሥልጠና ወስደው ተጠማቂያኑን በቋንቋ በየአከባቢያቸው በየቀበሌያቸው በ18 ጣቢያዎች ለ15 ቀናት የሞተር ሳይክል ኪራይና የመምህራኑን የተጠማቂያንን ምግብ በመቻል ቅድመ ጥምቀት ስልጠና እንዲሰጣቸው አድርጓል፡፡

እንዲሁም የበሸዳ ቅዱስ ዮሐንስ ቤተክርስቲያን በልዩ ሁኔታ በዚህ ጉዞ ተመርቋል፡፡ይህን ቤተክርስቲያን ያስገነባው የደቡብ ኦሞ ኮሚቴ ብቻ ሳይሆን በዲመካ የሚገኙ የህንጻ አሰሪ ኮሚቴ እንዲሁም በጅንካ በቱርሚ በአካባቢ የሚገኙ ምዕመናን በአደረጉት የጋራ ርብርብ ነው፡፡

የዚህም ቤተክርስቲያን ምረቃ ዕለት የሐመር ወጣቶች በቋንቋቸው መዝሙር ያቀረቡ ሲሆን በይበልጥም ደግሞ “ከበረሃመጣ” በሚል ርዕስ ወጣት ሻዳ በተኮላተፈ አማርኛ ያቀረበው ግጥም ብዙዎችን በእንባ ያራጨ ነበር፡፡

ከቤተክርስቲያኑ ምረቃ በኃላ በዚሁ ዕለት ማለትም ጥቅምት 26 ቀን 2010 ዓ.ም የሐመር ሻንቆ ቤተክርስቲያን የመሠረት ድንጋይ በሊቃነ ጳጳሳቱ ተቀምጧል፡፡

በዚህ ጉዞ ላይ ሶስት ሊቃነ ጳጳሳት ተገኝተው ስርዓተ ጥምቀቱን የቤተክርስቲያኑን ቡራኬ እና የመሠረት ድንጋይ ማስቀመጥ ስነ ስርዓቱን አከናውነዋል፡፡

የተገኙት ሊቃነ ጳጳሳት 

  1. ብጹዕ አቡነ ፊሊጶስ የደቡብ ኦሞ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል
  2. ብጹዕ አቡነ ዕንባቆም በቅድስት ሀገረ ኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት ሊቀጳጳስ የቅዱስ ሲኖዶስ አባል   
  3. ብጹዕ አቡነ ቀውስጦስ የሰሜን ሸዋና ሰላሌ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ናቸው፡፡

በተለይም ብጹዕ አቡነ ቀውስጦስ የበሸዳ ቅዱስ ዮሐንስን ቤተክርስቲያን ምረቃ በአል ላይ ታቦቱ ወጥቶ ትምህርት በሰጡበት ወቅት የእኔ የለገጣፎ ቅዱስ ዮሐንስ ታስሮብኛል እናንተን እግዚአብሔር ይሰማል ለእግዚአብሔር ቅርብ ናችሁ ጸልዩልን ያሉት አባባል ብዙዎች በእንባ አራጭቷል፡፡

የሻንቆ ቅዱስ ጊዮርጊስን ለመስራት የሠሰረት ድንጋይ በተቀመጠበት ወቅት በቦታው የተገኙ ከአዲስ አበባ እና ከአከባቢም ከመጡ ምዕመናን 70 ሺ በላይ ቃል የተገባ ሲሆን ኮሚቴው ይህንንም ቤተክርስቲያን በአጭር ጊዜ ጨርሰን ለእነዚህ ዘወትር ተስፋ በማድረግ ለሚጠባበቁ ወገኖቻችን ማስረከብ እንድንችል በሀገረ ውስጥ ሆነ በውጭ የሚገኙ ኦርቶዶክሳዊያን ምዕምናን በያሉበት አቅማቸው የፈቀደውን በማድረግ ከሰማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ ረድኤትና በረከት እንዲሳተፉ ኮሚቴው ጥሪ አቅርቧል፡፡

ከበረሃ መጣ

አምላክን ያጠመቀ በቅዱስ እጆቹ
በማኅጸን የሰገደ ባልጠኑ እግሮቹ
ሊፈልገን መጣ ሆነናል ልጆቹ
ከእንግዲህ አንፈራም እንማጸናለን
አምላከ ዮሐንስ ብለን እንድናለን
አምላከ ዮሐንስ ባንተ እናምናለን
ሰይጣንን ጠንቋይን በእውነት እንክዳለን
አሁን አንፈልግም ሌላ ደባል ነገር
አንድ አምላክ እግዚአብሔር በሰማይ በምድር
የድንግል ማርያም ልጅ በል አሁን ባርከን
ቤትህን ሰርተናል ከእኛ እንዳትለየን
ረሀብና ድርቁን በሽታ ቸነፈር
አንተን ጌታን ይዘን ከቶ ከእኛ አይኖር
ከእንግዲህ ይበቃል ወደዚህ እንሰብሰብ
ከበረሃው ንጉስ ከዮሐንስ እንቅረብ
የበረሃ አንበጣ በልቶ ጠፈር ቆዳ ለብሶ ያኔ የሰበከው
ይህው ከእኛ መሀል መጣ ቆዳ ከለበስነው በቆዳ ካጌጥነው
ኢየሱስን ያጠመከው ዮሐንስ ቅዱስ
ለምንልን ከአምላክ መንግስቱን እንውረስ
ከተሰራልን ቤት ስጋውን እንብላ ደሙንም እንጠጣ
በቀኙ እንዲያቆመን የድንግል ማርያም ልጅ ዳግመኛ ሲመጣ
ከበረሃ የነበረው በረሃውን የሚያውቀው
የዘካርያስ ልጅ የበረሃ ማር ምግቡ የነበረው
ይህው ከእኛ መንደር ከበረሃ መጣ
ዋስትና መድኅን መጠጊያ እንዳናጣ
ሐመር በሸዳችን እንኳን ደስ አለሽ
ሶስት ጳጳሳት በአንዴ ባረኩሽ
ከእንግዲህ አንመለስ እኛ ወደኃላ
ወደፊት ነው እንጅ ከጽድቁ እንብላ
እንግዲህ አደራ አባቶች እንስጣችሁ
ካህን መድቡልን አትተውን ባካችሁ
ካህናት ከሌሉበት መቅድስ መቼ ያምራል
ሳይከፈት ውሎ እንዴት ቤቱ ያድራል
ጠዋትና ማታ ከደጁ እንውደቅ
ብንታመም እንኳን በእርሱ እንድንፈወስ
ካህን መድቡልን ከአምላክ የሚያስታርቅ
መስቀልን አሳልሞ ከኃጢአት የሚያላቅቅ
አደራ አደራ አደራ አባቶች ካህን መድቡልን
ከእራሳችን ካህን አምላክ እስኪያወጣልን፡፡

ጥቅምት 26/2010
ግጥም ዲ.ን አበባየሁ ፈቃዱ
ንባብ ወጣት ሻዳ ኮሌ